General staff meeting

የኮሌጃችን መሰረታዊ የመምህራን ማህበር ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የሥራ ሪፖርት በማዳመጥ የዓመቱ ዕቅድ በማጽደቅ ፣የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ አደረገ፡፡

ወ/ሶ/ግ/ኮ ታሕሳስ 11፣ 2017 ዓ/ም

የኮሌጃችን መሠረታዊ መምህራን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ያካሄደ ሲሆን በጉባኤውም የሥራ ሪፓርትና 2017 ዓ/ም ዕቅድ ላይ ገለጻና ውይይት እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ አካሂዷል፡፡በመድረኩ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሌጃችን ዲን ዶ/ር አሉላ ታፈሰ፣ የጉባኤው ታዳሚዎች እንኳን ለጠቅላላ ጉባኤ አደረሳችሁ በማለት፣ምቹ የሆነ የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመፍጠር ጠንካራ ማህበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ቀድሞ የማህበሩ ሊቀ-መንበር መ/ር ዳህላክ ጨመሰ የማህበሩ ሥራ ሪፖርትና 2017 ዓ/ም ዕቅድ ላይ ለጉቤኤው ገለጻ አድርገዋል፡፡

በቀረበው የሥራ ሪፖርትና ዕቅድ መነሻ በመድረኩ ዕድል የወሰዱ የማህበሩ አባላት ለኮሌጃችን ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረታዊ ማህበሩ ስላበረከተው አስተዋጽኦ በማመስገን፤የመምህራን ጥቅምን ለማስከበር፣የመማር ማስተማርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማህበሩ ስለሰራቸው ተግባራት በተመለከተ ጥያቄና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ሰፋ ያለ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል ፡፡

ከውይይቱ በኋላ የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን ከጉባኤው ከተጠቆሙ መካከል አብላጫ ድምጽ ያመጡ መ/ራን ተመርጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት፡-መ/ርት ብርቱካን ኢሳያስ የማህበሩ ሊቀ-መንበር፣ መ/ር ክሩቤል ተስፋዬ ዋና ፀሐፊ፣ መ/ርት ሊድያ ቦጋለ ሥርዓተ-ጾታ፣ መ/ር ንጋቱ ማርቆስ ገንዘብ ያዥና መ/ር እሸቱ ጳውሎስ ሂሳብ ሹም በመሆን ተመርጠዋል፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ በመሆን አዲስ የተመረጡት መ/ርት ብርቱካን ኢሳያስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ጉባኤው እኔን አምኖ እስከመረጠኝ ድረስ ዘር፣ቀለምና ሀይማኖት ለይቼ አድሎ ሳላደርግ ሁሉንም አባላት በእኩልነት አገለግላለሁ ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የኮሌጃችን ዲን ዶ/ር አሉላ ታፈሰ በመድረኩ ማጠቃላያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ኮሌጃችን የተሻለ መስመር እንዲያዝ ስላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡

የክልሉ መምህራን ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ካሳ ለጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት፣የመሰረታዊ ማህበሩ አባላት ለእውነት የሚሰሩ አመራሮችን በማግኘታቸው ዕድለኞች እንደሆኑ በማመላከት፤ከጎናቸው ሆነው መደገፍ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *