ኮሌጃችን 1243 ተማሪዎችን ዕለት አስመረቀ

ኮሌጃችን በስድስቱ የሙያ መስኮች በመካከለኛ ደረጃ ያሰለጠናቸውን 1243 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመረቀ።
ወ/ሶ/ግ/ኮ ሀምሌ 5/ 2017 ዓ/ም

ኮሌጃችን በሰብል ልማት፣ ተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ፣ እንስሳት ጤና፣ መስኖ እና ፍሳሽ፣ እንስሳት እርባታ እና ሕብረት ሥራ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት የሙያ መስኮች ትምህርታቸውን በንድፈ-ሃሳብና በተግባር በሚገባ ተከታትለው ያጠናቀቁ 1243 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

ኮሌጃችን በዛሬው ዕለት በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይልን ያስመረቀው ለ23ኛ ዙር ሲሆን፣ ባለፉት 22 ዙሮች ያስመረቃቸውን ጨምሮ ከ28 ሺህ በላይ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠኑ የግብርና ባለሙያዎችን በማስመረቅ ለአገራችን ብሎም ለክልላችን ግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በምረቃው ላይ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የዋንጫና ልዩ ሽልማት ተበርክቷል።ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል የላቀ ውጤት ላስመዘገበው ተማሪ ግርማ አለማየሁ የወርቅ ሜዳሊያ፣ዋንጫና ልዩ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ከሴት ተማሪዎች መካከል የላቀ ውጤት ላስመዘገበችው ተማሪ ምህረት ሳሙኤል የወርቅ ሜዳሊያ፣ዋንጫና ልዩ ሽልማት ተበርክቶላታል።

በምረቃው ላይ በቢሮ ኃላፊ ማዕርግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋና ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የኮሌጃችን አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢና የዕለቱ ክቡር ዕንግዳ አቶ ጋንታ ጋምአ፣ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳደር ጽ/ኃላፊና የዞኑ ዋና አስተዳደሪ ተወካይ አቶ ወንድሙ ደረጀ፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ማኔጅመንት አባላትና የኮሌጃችን አስተዳደር ቦርድ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የዞንና ክልል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኮሌጃችን አካዳሚክ ኮሚሽንና ማኔጅመንት አባላት፣ መምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች ተገኝተዋል።

ከምረቃው በኋላ በምረቃው ላይ የተገኙ ዕንግዶች፣የኮሌጃችን አካዳሚክ ኮሚሽንና ማኔጅመንት አባላት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

ውድ ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ!